ሰቆቃ በማዕከላዊ – አበበ ካሴ (ነገረ ኢትዮጵያ)

July 15, 2015

‹‹እጄን ወደ ላይ አስረው ብልቴ ላይ ሀይላንድ አንጠልጥለውበታል፡፡ ሴቶቹ ሀይላንዱን የሚበቃቸውን ያህል ያወዛውዙታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ የዘር ፍሬየን ከጥቅም ውጭ አድርገው ዘሬን እንዳልተካ አድርገውኛል፡፡ ሽንቴንም መቆጣጠር አልችልም፡፡››

Ethiopian prisoner tortured in Kality

አበበ ካሴ

እኔ አበበ ካሴ እባላለሁ፡፡ የሰሜን ጎንደር ተወላጅ ነኝ፡፡ በማዕከላዊ እስር ቤት ከ5 ወር በላይ ታስሬለሁ፡፡ ከዚህ መካከል 4 ወር ከ25 ቀናት በጨለማ ቤት ተቆልፎብኝ ቆይቻለሁ፡፡

ማዕከላዊ በነበርኩበት ወቅት የሁሉም እግርና እጆቼ ጥፍሮች ተነቅለዋል፡፡ አንዳንድ ቀን እጄ ላይ የሆነ ነገር ስለሚወጉኝ ጥፍሮቼ ሲነቀሉ አላውቅም፡፡ ስነቃ ነው መነቀላቸውን የማውቀው፡፡ ከዛም ቁስሉን እየነካኩ ያሰቃዩኛል፡፡ ማደንዛዣ ለምን እንደሚወጉኝ አላውቅም፡፡ ጥፍሮቼን ሲነቅሉኝ ብቻ ሳይሆን ሌላ ጊዜም ራሴን እንድስት ያደርጉኛል፡፡ እጅና እግሬን አስረው እንደ ፍሪጅ ያለ እቃ ውስጥ ያለ በረዶ ውስጥ ያስቆሙኛል፡፡ ለብዙ ሰዓት በጣም ቀዝቃዛ የሆነ ቦታ ላይ እስክደነዝዝ ቆሜ እውላለሁ፡፡ እስኪበቃቸው ከደበደቡ በኋላ እጅና እግሬን አስረው ከምርመራ ክፍሉ በታች በሚገኝ ምድር ቤት ክፍል ውስጥ ያለ ጉድጓድ ላይ ጥለውኝ ይሄዳሉ፡፡ ጉድጓዱ ጉንዳንን ጨምሮ ተባዮች ያሉት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እግሬንና እጄን አስረው ዘቅዝቀውኝ ይሄዳሉ፡፡ የመጣው ሁሉ ዝዋዥዌ እንደሚጫወት ህፃን ወዲያና ወዲህ ያደርገኛል፡፡ ገልብጠው አስረው ሲዘቀዝቁኝ በአብዛኛው ራሴን እስታለሁ፡፡ እግርና እጄን ከወንበር ጋር ያስሩኛል፡፡

ከወንዶች በተጨማሪ ሴቶችም ይመረምሩኛል፡፡ ሴቶቹ የሚመረምሩኝ ራቁቴን አርገው ነው፡፡ እነሱም ራቁታቸውን ሆነው ነው የሚመረምሩኝ፡፡ አሁን ለመናገር የማልደፈርው አፀያፊ ነገርም ፈፅመውብኛል፡፡ ይህን አፀያፊ ነገር የሚፈፅሙት አደንዛዥ እፅ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ በአይኔ አይቻቸዋለሁ፡፡ መርማሪዎቹ ሰውነቴን በኤሌክትሪክ አቃጥለውኛል፡፡

ኤሌክትሪኩን የሚሰኩት ደረቴና የውስጥ እግሬ ላይ ነው፡፡ በዚህም የውስጥ እግሬ ተገልብጦ ሌላ ሰውነት አምጥቶ ነበር፡፡ እጄን ወደ ላይ አስረው ብልቴ ላይ ሀይላንድ አንጠልጥለውበታል፡፡ ሴቶቹ ሀይላንዱን የሚበቃቸውን ያህል ያወዛውዙታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ የዘር ፍሬየን ከጥቅም ውጭ አድርገው ዘሬን እንዳልተካ አድርገውኛል፡፡ ሽንቴንም መቆጣጠር አልችልም፡፡ ይህን ያህል አሰቃይተው ከጥቅም ውጭ ስሆን ቂሊንጦ አምጥተው ጣሉኝ፡፡ 11 ወር ያህል አልጋ ላይ ነበርኩ፡፡ በኤሌክትሪክ ግርፊያው ምክንያት ግራ ሰውነቴ ሽብ ሆኖ ነበር፡፡ ግራ እግሬ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር፡፡ በምርኩዝ ነበር የምሄደው፡፡ አሁን እያነከስኩ ነው የምሄደው፡፡

በተለይ ማዕከላዊ ውስጥ ይህን ያህል የሚሰቃዩኝ አንደኛ የሚያግዛችሁ አገር ማን ነው በሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ እንድትንቀሳቀሱ የሚተባበሯችሁን የብአዴን ባለስልጣናት ስም ተናገር እያሉ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የሚያሰቃዩኝ የት የት ቦታ ነው የሰለጠንከው እያሉ ነው፡፡

እዚህ ቂሊንጦ ከመጣሁ በኋላም ያሰቃዩኛል፡፡ ወጣቶች እንዳይቀርቡኝ ያስፈራሩዋቸዋል፡፡ ማንም ጠርቶ እንዳይጠይቀኝ እየተደረገ ነው፡፡ ጨለማ ክፍል ወስደውም አስረውኝ ያውቃሉ፡፡ እነሱ ደብድበው ከጥቅም ውጭ ካደረጉኝ በኋላ የምደገፍበትን ምርኩዝም ቀምተውኛል፡፡ ‹‹ይህኮ የጦር መሳሪያ አይደለም፡፡ እንጨት ነው፡፡ ለምን ትቀሙኛላችሁ? ደግሞም እናንተ ናችሁ እንዲህ ያደረጋችሁኝ፡፡›› ብያቸው ነበር፡፡ የሚሰሙ ሰዎች አይደሉም፡፡ የታሰርኩበት ክፍል ውስጥ እንድተኛበት የተሰጠኝ ቦታ ሽንት ቤቱ አጠገብ ነው፡፡ ሽንት እየሸተተኝ ነው የምተኝው፡፡ ‹‹ወደ ሌላ ቦታ ቀይሩኝ!›› ስላቸው ‹‹ደግሞ ለአንተ ይህ አንሶህ ነው?›› ይሉኛል፡፡ ያ ሁሉ ድብደባ ደርሶብኝ አልጋ ላይ በነበርኩበት ወቅት ወጣቶቹ ህክምና እንዳገኝ ወደ ሀኪም ቤቱ ወሰዱኝ፡፡ እነሱ ግን ‹‹ለአንተ ህክምና ሳይሆን ጥይት ነበር የሚገባህ›› ብለው መለሱኝ፡፡ እንዲህ እያሉ ለምን እንደማይገድሉኝ ይገርመኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ልጆችዋ ለእልቂት፣ ለስደት፣ ለግድያ እየተዳረጉ ነው፡፡ በአካልም ሆነ በስነ ልቦና ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ዓለም ለሰው ልጅ ምቹ በሆነችት ከዓለም ውጭ ሆነናል፡፡ የመገናር፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት በአጠቃላይ ሰው የሚያደርጉንን መብቶች ተነጥቀናል፡፡ ከሰው የማንቆጠርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ገዥዎቻችን ህዝብን እየገደሉና ከሰው በታች አድርገው እየገዙም ቢሆን ግን ዓለምን እያታለሉ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሁሉ የሚደረገው የአንድን ቡድን የበላይነት ለማስፈን መሆኑ ነው፡፡ እንዲጠፋ ሆን ተብሎ ጥቃት የሚደርስበት ህዝብም እንዳለ እያየን ነው፡፡ ግን ኢትዮጵያ የ95 ሚሊዮን ህዝን ሀገር ናት፡፡

አሁን ያለው ስርዓት የአንድ ቡድን ስርዓት ነው፡፡ ለእሱ መኖር ደግሞ ሌሎቹን ገድሎ፣ አሰቃይቶ፣ አሳድዶ መኖር ይፈልጋል፡፡ ለስሙ የብሄር ብሄረሰብ መብት እናከብራለን ቢባልም እውነቱ ግን ኢትዮጵያውያን የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀትና ሌሎች መብቶችን ተነፍጎ ከሰውነት ወጥተው ይገኛሉ፡፡ በዓለም ደረጃ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ቋንቋና ዘርን አይለይም፡፡ ይህ የሚደረገው በህወሓት ስርዓት ብቻ ነው፡፡ እኔ በርካታ ሰቆቃ የደረሰብኝ ሰው ስለሆንኩ ስርዓቱ የሚፈፅመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመመስከር እችላለሁ፡፡ እኔን ሰቆቃ ያደረሱብኝ ሰዎች ማንነታቸው መታወቅ ስላለባቸው እንደሚከተለው ስማቸውን እዘረዝራለሁ

1. አቶ አሸነፍ ተስፋሁን ላቀው
2. አቶ አብርሃም አይሸሽም
3. ሙሉጌታ ወርቁ
4. አቶ ደረሱ አያናው
5. የአማራ ክልል ደህንነት ኃላፊ የሆነው አቶ ተሾመ
6. የሰ/ጎ/መ/የታክቲክ ኃላፊ አቶ ሙላ እንየው
7. የማዕከላዊ ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ተክላይ
8. የማዕከላዊ ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ጌትነት
9. አቶ አሰፋ አትንኩት (ምርመራበ ኃላፊ)
10. መቶ አለቃ ተስፋዬ (መርማሪ)
11. ሳጅን ፍሬ ህይወት (መርማሪ)
12. ሳጅን ፅጌ (መርማሪ)

ከላይ የጠቀስኳቸውን በስምና በአካል የማውቃቸው ሲሆኑ ከእነዚህ በተጨማሪ ከደህንነት መስሪያ ቤቱ እየመጡ የሚያሰቃዩን ስማቸውን የማላስታውሳቸውና በመልክም የማውቃቸው የህወሓት ደህንነቶች አሉ፡፡

እዚህ እኛን እንደዚህ ሲያሰቃዩ ሀገሪቱን ገንዘብ መዝብረው የታሰሩ ሰዎች ምንም አይሆኑም፡፡ ተመችቷቸው ነው የሚኖሩት፡፡ ቂሊንጦ ውስጥ ሰው እንዳይቀርበኝም ቢፈልጉም ሰው ግን በጣም ይወደኛል፡፡ አሁን ጥፍሮቼ በቅለዋል፣ መራመድ ችያለሁ፡፡ አንድ ሽህ አመት አይኖርም፡፡ በጣም ብዙ ወገኖቻችን ሞተዋል፡፡ እኔ አለሁ፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ባለስልጣናት እኔ ላይ የደረሰውን ጨምሮ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ በፈፀሙት ወንጀል መጠየቃቸው የማይቀር ነው፡፡

ይህ ሁሉ በደል ደረሰብኝ ስል ዝም ብዬ አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው መጥቶ የተሸማቀቀውን እግሬን፣ ቅጥ ባጣ ድብደባ የተጎዳው ሰውነቴን ማየት ይቻላል፡፡ ጥፍሮቼንም ለመስክርነት ይዤያቸዋለሁ፡፡ እነሱ ነቅለው ጥለው ሲሄዱ እኔ ስነቃ ሰብስቤ አስቀምጣቸዋለሁ፡፡ የተወሰኑትን ለመረጃነት አስቀምጫቸዋለሁ፡፡ ይህን ስል ግን እኔ ላይ የደረሰው ስቃይም የማይጠበቅ ሆኖ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች እንኳንስ ግለሰብ ሀገርም ገንጥለዋል፡፡ ከ40 አመት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ካርታ ተሸርፏል፡፡ እንኳን ሰው ሀገርም ለማጥፋት እየሰሩ ነው፡፡

ታሪካቸው፣ አመጣጣቸውም የሚያሳየው ይህን ነው፡፡ ይህን ሁሉ የምለውም መታወቅ ስላለበት ነው፡፡

Advertisements
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s