ጋዜጠኞቹና ጦማርያኑ ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሦስቱ ጋዜጠኞችና ስድስቱ ጦማሪያን ዛሬ በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ሁሉም በተከሰሱባቸው ክሶች <<ጥፋተኞች አይደለንም>> ብለዋል።

የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ያደመጠው ፍርድ ቤትም፤ ለፊታችን መጋቢት 21 ቀጠሮ በመስጠት የእለቱን ችሎት  አጠናቋል፡፡

ተከሳሾቹ እጃቸው ከተያዘበት ከሚያዚያ ወር 2006 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከቆዩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ክስ የተመሰረተባቸው ጥር 28 ቀን 2007 ሲሆን፤  ለመጀመሪያ ጊዜ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት እድል ያገኙት ግን በዛሬው ዕለት ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤  የጦማርያኑን ችሎት በመሀል ዳኝነት ሲያስችሉ የነበሩት አቶ ሸለመ በቀለ ተከሳሾቹ <<ይቀየሩልን>> ባሉት መሰረት ሐሙስ ጥር 28 ቀን 2007 ዓ.ም ራሳቸውን በፈቃደኝነት እንዳገለሉ የተገለጸ ቢሆንም፤ በዛሬው ችሎት ላይ ግን ቀርበው እንደነበር -ፍርድ ቤት ተገኝተው ችሎቱን የተከታተሉት የተከሳሽ ጓደኞችና ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡

This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a comment